የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን ማንሠራራት ወደ ዘላቂ ብልጽግና ለማሻገር በቁርጠኝነት ይሰራል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By sosina alemayehu

September 07, 2025

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰላማችንን እያጸናን የኢትዮጵያን የማንሠራራት ጉዞ ለማፋጠን በተባበረ አቅም መትጋት አለብን አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

በዛሬው ዕለት እየተከበረ የሚገኘውን የኅብር ቀን አስመልክቶ “ሰላማችንን ማጽናት ለኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገራዊ መድረክ ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ 2017 ዓ.ም የሕዳሴ ግድብ የተጠናቀቀበት፣ ማዳበሪያ ለማምረት ስምምነት የተደረገበት፣ የኮሪደር ልማት፣ የአረንጓዴ ዐሻራና ሌሎች ታላላቅ ሥራዎች የተከናወኑበት ነው ብለዋል።

የተገኙ እመርታዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ዘላቂ ሠላምን ማጽናት አስፈላጊ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ጥለት ህብረ ቀለምና ባለ ብዝኃ ፀጋ ሀገር ናት ፤ የቋንቋ፣ የባሕል፣ የእምነት፣ የታሪክ፣ የአመለካከትና የጾታ ልዩነት ውበቷና ዕሴቷ ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡

ፀጋዎቻችንን ለብልፅግና ጉዟችን ለመጠቀም “የዘመናት ሾተላይ” ሆኖ የኖረውን የግጭት አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰብረን መጣል የምንችልበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት የምናስመዘግብበት ዘመን ላይ እንገኛለን ነው ያሉት፡፡

የግጭት አዙሪት ምንጭና የብልጽግና ዕንቅፋት የሆኑትን የውጭ ባዳና የውስጥ ባንዳ ለማስወገድ በአንድ እጃችን የብልጽግና ጉዟችንን ማሳለጥ በሌላ እጃችን ደግሞ ሰላማችንን በፅኑ መሰረት ላይ ማፅናት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ማንሠራራት መጀመሩን እና የዘመናት ስብራቶቿ እየተጠገኑ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ለሁላችን የምትሆን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጸና ኢትዮጵያን ለመገንባት አመራሩ የማስጠበቅ፣ የማጽናት፣ የማሣለጥ እና የማቀናጀት ተግባራትን ሳይቆራረጡ በቀጣይነት በአግባቡ ሊፈጽሙ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴርና ባለ ድርሻ አካላት ሰላምን ተቋማዊ በማድረግ ወደ ዘላቂ ሰላም የምናደርገውን ጉዞ የመደገፍ ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡