አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2017 (ኤፍ ኤምሲ) በአሁኑ ወቅት ዓለምን እየፈተነ ለሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች አንድ ሀገር ብቻውን መፍትሔ አያመጣም ስለማያመጣ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ተጠየቀ።
2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ መክፈቻ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ጉባኤው ‘ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማሳለጥ፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ’ በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።
በጉባኤው መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ የጥንካሬ እና የአንድነት ተምሳሌት ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ርዕይን ወደተጨባጭ ተግባር በመቀየር ረገድ አረዓያ መሆኗን አንስተዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ ፈተና አንድ ሀገር ብቻውን መፍትሔ ሊያመጣ ስለማይችል እጅ ለእጅ ተያይዞ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የአፍሪካውያን ድምፅ በዓለም መድረኮች መሰማት በመጀመሩ የዜጎችን ህይወት የሚለውጡ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ጠቅሰው፤ አህጉራዊ የፋይናንስ ተቋማትን በማጠናከር የአረንጓዴ ልማትን መደገፍ ይገባል ብለዋል።
የአህጉሪቱ ስኬት በአፍሪካውያን የራስ ጥረት እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢውን ቦታ በመስጠት እውን ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ የግብርና እና ኢንዱስትሪ ልማትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ተደጋጋሚ ድርቅን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ መሆኗን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመዋጋት መንግስታቸው ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ይህ ጉባዔ ለአንገብጋቢው የአየር ንብረት ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ለጉባኤው አዘጋጆች ምስጋና አቅርበዋል።
የአፍሪካ የአየር ንብረት አጀንዳን ሀገራቸው እንደምትጋራው በመግለጽ፤ ታዳሽ ኃይል ተደራሽነት ላይ ያለውን ተግዳሮት በመፍታት በትኩረት እንደሚሰራበት ጠቁመዋል።
የድርቅ ተፅዕኖን ለመታገል የሸበሌ እና ጁባ ወንዞችን በመጠቀም የምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሀገሪቱ ያላትን ውሃማ አካላት በመጠቀም የምግብ ስርዓት ለማሻሻል ጥረት መጀመሯንም አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ፍትሀዊ፣ ውጤት የሚያመጣ እና የሚተነበይ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ይህ ጉባኤ አፍሪካ አቋሟን በግልጽ የምታንጸባርቅበት መሆኑን ገልጸዋል።
መሳፍንት ብርሌ