የሀገር ውስጥ ዜና

ደቡብ ሱዳን ከሕዳሴ ግድብ ኃይል ለማግኘት በቅርቡ ስምምነት ትፈፅማለች – ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር

By Mikias Ayele

September 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ደቡብ ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ለማግኘት የሚያስችል ስምምነት በቅርቡ ትፈፅማለች አሉ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት፡፡

ፕሬዚዳንቱ በሕዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ታላቅ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ተገንብቶ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ የቀጣናውን ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ በቅርቡ ሀገራቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትፈፅም ጠቁመዋል።

ይህም በደቡብ ሱዳን ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ከተሞች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እንደሚፈታ ገልጸው÷ ግድቡ ለደቡብ ሱዳን ህዝብ አዲስ ምዕራፍን የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ሁለቱን ሀገራት በኃይል መሰረተ ልማት የሚያስተሳስር እና የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ