የሀገር ውስጥ ዜና

ግድቡ ለመላው አፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ነው – ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

By Yonas Getnet

September 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመላው አፍሪካ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉ ተምሳሌት የሚሆን ነው አሉ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ።

ፕሬዚዳንቱ በግድቡ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ግድቡ የምህንድስና ስራ ብቻ ሳይሆን አፍሪካ የራሷን ዕጣ ፋንታ መወሰን እንደምትችል የሚያሳይና ብልጽግናዋን እንድታረጋግጥ የሚያነሳሳ ፕሮጀክት መሆኑን አውስተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ብሎም የተፋሰሱን ሀገራት አንድ የሚያደርግ ወንድማማችነትን፣ ትብብርና የጋራ ራዕይን ያጠናክራል ነው ያሉት፡፡

ኬንያ ቁልፍ አጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ጎን መራመዷን ቀጥላለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የአንድ ሀገር ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካኒዝም መገለጫ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ግድቡ አፍሪካ መር የሆነ የመሰረተ ልማት ግንባታን ለማስፋፋት የሚያነሳሳ ብሎም የአፍሪካ ሕብረትን አኅጉሩን በኤሌክትሪክ ኃይል የማገናኘት ርዕይ የሚደግፍ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ሰፊ የሆነ የታዳሽ ኃይል እምቅ አቅም ያላት አፍሪካ በሕዝብ ቁጥር መጨመርና በከተሞች መስፋፋት ምክንያት የኢነርጂ ፍላጎቷ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ይህም በዘርፉ ላይ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት በእጥፍ ማሳደግ የሚጠይቅ እንደሆነ ገልጸው፥ ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመላው አፍሪካ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉ የሚያደርግ ተምሳሌት ነው ብለዋል።

ኬንያ በፈረንጆቹ 2022 ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት መጀመሯን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፥ ለ25 ዓመታት የሚቆይ ስምምነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በኢነርጂ ዘርፍ እያደረጉት ለሚገኘው ትብብር ህያው ምሳሌ እንደሆነ አመልክተዋል።

በተጨማሪም ኬንያ ከታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት የሚያስችላት ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፥ ሀገራቸው በ2030 የልቀት መጠንን ዜሮ ለማድረስ ለያዘችው ዕቅድ ትልቅ አስተዋጽዖ እንድሚያበረክትም አስረድተዋል።

ለዚህ ታሪካዊ ስኬት የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግስት እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ለእኛም ጭምር መነሳሳት የሆኑ ተግባራትን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት