አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከኦሮሚያ ሶቨሪን ፈንድ እና ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር የተደረሰው የልማት ስምምነት ታላቅ ርምጃ ነው አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
የክልሉ መንግስት ከሁለቱ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ስምምነቱን አስመልክቶ እንዳሉት፤ ከተቋማቱ ጋር የተደረሰው ስምምነት ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ላይ ለመስራት ያስችላል።
በተጨማሪም የማዕድን ዘርፍ እና የመሳሰሉት ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ስምምነት ልማትን ከማፋጠን አንጻር የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ መንግስት ልማትን ለማጎልበት ጠንካራ አቋም እንዳለው ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ሶቨሪን ፈንድ ላይ የተሰራው ሪፎርም የግሉ ዘርፍ ከመንግስት ጋር አብሮ የመስራት ፍለጎትን መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡
በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ኬኛ በቨሬጅስ የሪፎርሙ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የተደረሰው ስምምነት ክልሉ ያለውን የልማት እድልና አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል፡፡