የሀገር ውስጥ ዜና

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

By Abiy Getahun

September 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች 2018 አዲስ ዓመትን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በመልዕክታቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ መቻላችን በአንድነት ከቆምንና በጋራ ከተጋን በሁሉም አሸናፊ መሆን እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል።

ሰላም ለማረጋገጥና የልማት ስራዎችን ለማከናወን በተደረገው የተቀናጀ ርብርብ ስኬት መመዝገቡን ገልጸው፤ በ2018 ዓ.ም ዘላቂ ሰላም በማስፈን እና ልማትን በላቀ ደረጃ በመፈጸም የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በተመረቀበት ማግስት የምንቀበለዉ አዲሱ ዓመት ተስፋ ሰንቀን የምንሸጋገርበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ማንሰራራት ዘመን እየተሸጋገረች የምትገኝበት ምዕራፍ በመሆኑ አዲሱ ዓመት በአጠቃላይ ጊዜያችንን፣ እዉቀታችንን፣ ጉልበታችንን፣ ፀጋዎቻችንን ፣ የሕዝብ ዐቅሞችን፣ የመልማት እምቅ ዕድሎችን በመጠቀም ለእመርታዊ ለዉጥ የምንተጋበት ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳዳር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ የወንድማማችነትን ትርክት አጉልተን በጋራ እንደግ ባህላችን በውስጥ አንድነታችን ለታላላቅ ስኬቶች የምንዘጋጅበት አዲስ ዓመት ይሆናል በማለት ተናግረዋል።

ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻል እና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዘውን ራዕይ እውን ለማድረግ በጽናት፣ በትጋትና በህብረት መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ አዲሱ ዓመት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን የምናስመርቅበት እና የምንጀምርበት በመሆኑ ደስታችን ታላቅ ነው ብለዋል።

የህዳሴ ግድባችን አንድነት ኃይል መሆኑን አሳይቶናል በማለት ገልጸው፤ መተሳሰብና ለዓላማ በጋራ መሰለፍ ወደ ታለመ መዳረሻና ግብ የሚያደርስ ድልድይ መሆኑን በመረዳት የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ፤ ኢትዮጵያ የ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመትን በታላላቅ ድሎች ታጅባ እየተቀበለች ነው ብለዋል።

በአንድነት ቆመን፤ ፈተናዎችን በጋራ ተሻግረን ለፍፃሜ ያበቃነው የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ፈተና ተሻግረን ያቀድነውን ማሳካት የምንችል ህዝቦች መሆናችንን ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።

በግብርና፣ በማዕድን እና በሌሎችም መስኮች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው ለቀጣይነቱ በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በህዳሴ ግድባችን የግንባታ ሂደት የተሻገርነውን ከባድና ውስብስብ ፈተና በልባችን አትመን ለቀጣይ ራዕያችን መወጣጫ መሰላል አድርገን መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

አዲሱ ዓመት ጥላቻ በፍቅር፣ መገፋፋት በመቀራረብ፣ ጥርጣሬ በመተማመን፣ መከፋፈል በአንድነት፣ ስንፍና በትጋት፣ ድህነት በብልፅግና የሚቀየርበት ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል።