የሀገር ውስጥ ዜና

በሐረር ከተማ ለአካባቢ ዘላቂ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል – አቶ ኦርዲን በድሪ

By abel neway

September 13, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረር ከተማ የወንዝ ዳርቻ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ ለአካባቢ ዘላቂ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ።

የሐረሪ ክልል መስተዳድር ም/ቤት በሐረር ከተማ በሚገኙ ወንዞች ላይ የወንዝ ዳርቻ ልማት ማከናወን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።

የወንዝ ዳርቻ ልማቱ 800 ሜትር ርዝመትና 80 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን÷ በ6 ሔክታር መሬት ላይ እንደሚከናወን በከተማዋ ማዘጋጃ ቤት በቀረበው ዲዛይን ተመላክቷል።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በዚህ ወቅት ÷በከተማው የሚገኙ ወንዞች ከብክለት የጸዱ፣ ውብና ማራኪ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ልማት ለነዋሪው ጤናማ ሕይወት እና ለአካባቢ ዘላቂ ልማት ወሳኝ አስተዋፅኦ ከማበርከቱ ባለፈ የከተማዋን ገጽታ የመቀየር አቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከተማዋ ንጹህ ወንዞች የሚፈሱባት፣ ጽዱና ውብ እንድትሆን በማስቻል ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ነው የገለጹት።

ይህን እውን ለማድረግም ከመኖሪያ ቤቶች የሚወጡ ፍሳሾችን በሥርዓቱ ለማስወገድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንዲገባ አቶ አርዲን በድሪ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡