የሀገር ውስጥ ዜና

የሸካቾዎች የእውነት መንገድ… ዎራፎ

By abel neway

September 13, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአያሌ ዓመታት ሸካቾዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር ከቱባው ባሕላቸው በተቀዳ ሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ሲሻገሩ ኖረዋል።

በማስተዋል ችግርን ሲሻገሩ ከኖሩበት ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል እውነትን ለማግኘት የሚሄዱበት የአውጫጭኝ ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ ዎራፎ ይባላል። ዎራፎ የሸከቾዎች የችግር መፍቻ ጥበብና የእውነት መንገድ ነው።

ዎራፎ የሚለው ቃል ትርጉሙ አንድ ሰው ጥሩ ሰው ነው፤ የተከበረ ወይም እንከን የሌለበት ሰው ነው ብሎ ምስክርነት መስጠት ነው ይላሉ የብሄረሰቡ ባሕል አዋቂ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ማሪቶ።

ዎራፎ በዋናነት በሸካቾዎች የአውጫጭኝ ሥርዓት ያጠፋውን ጥፋት ከሌለበት ለመለየትና እውነትን ፈልጎ ለማግኘት ጥቅም ላይ ይውላል። በሸካቾዎች ዘንድ ምግባር ዋጋው ከፍ ያለ ነውና የከፋ ችግር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።

ነገር ግን በአጋጣሚ አንዳች ችግር ቢከሰት ዎራፎ ከችግሩ መነሻ (እውነት) ያደሳል ይላሉ አቶ ብርሃኑ ማሪቶ።

ለምሳሌ የድንበር ግጭት ቢከሰት ወይም ከቀፎ ማር ቢጠፋ ችግሩ የሚፈታው በዎራፎ የአውጫጭኝ ሥርዓት ነው።

የሀገር ሽማግሌች ወይም የጎሳ መሪዎች ጥፋቱ በተፈጸመበት መንደር ያሉ ሰዎችን ዛፍ ስር እንዲሰበሰቡ ያደርጋሉ።

የተሰበሰቡ ሰዎችም ተራ በተራ እየተነሱ ይቆማሉ ቀሪዎቹ ተሰብሳቢዎች ድምፅ እንዲሰጡ ይደረጋል፣ በዚህ ወቅት ጥፋተኛውን ለመለየት ሶስት ዓይነት የድምጽ አሰጣጥ ይኖራል ነው ያሉት፡፡

በአውጫጭኝ ሥርዓቱ አንድ ሰው ቆሞ ተሰብሳቢዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “ዎራፋ” ካሉ ይህ ሰው ምስጉን ነው። በጥፋቱ የለበትም ማለት ነው።

ሁለተኛ የድምጽ አሰጣጥ ወይም እውነትን የመፈለግ ሥርዓት ከፊል ወራፎ ነው። የመንደሩ ሰዎች ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው “ዎራፋ” ካሉ። ያ የቆመው ሰው በጥፋቱ እጁ ሊኖርበት ይችላል የሚል ጥርጣሬ አለ የሚል ትርጉም አለው።

የከፊል ወራፎ ድምፅ የተሰጠው ሰው ራሱ በቀጥታ ጥፋተኛ ባይሆንም ከቤተሰቦቹ አንዱ ተጠርጣሪ እንደሆነ የመንደሩ ሰዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

የመንደሩ ተሰብሳቢዎች ድምጽ እንዲሰጡ ሲጠየቁ መልሳቸው ዝምታ ከሆነ፣ ያ ሰው በቀጥታ ጥፋተኛ መሆኑ የተረጋገጠ ይሆናል።

የሀገር ሽማግሌዎች በአውጫጭኝ ሥርዓቱ በችግሩ እጁ አለበት የተባለውን ሰው ለብቻ እንዲቀመጥ ካደረጉ በኋላ የመንደሩ ሰዎች ያንን ሰው በምን ምክንያት በጥፋተኝነት እንደፈረጁት ተሰብሳቢውን ይጠይቃሉ።

የመንደሩ ሰዎችም ከምን ተነስተው ጥፋተኛ እንደሆነ የጠረጠሩበትን ምክንያት በበቂ ማስረጃ አስደግፈው ያብራራሉ።

የመንደሩ ሰዎች ያቀረቡት ማስረጃና ምክንያት ለሀገር ሽማግሌዎቹ ፍርድ ብቻውን በቂ አይሆንም። በጥፋቱ እጁ አለበት ተብሎ የተጠረጠረውን ሰው ጥፋቱን ስለመፈጸሙና አለመፈጸሙ እውነታውን እንዲናገር ዕድል ይሰጡታል።

እውነታውን መናገር የተጠርጣሪው ብቸኛው አማራጭ ነው ፤ እውነታውን መካድ የማይታሰብ ነው ፤ ምክንያቱ እውነቱን ከደበቀ ከአካባቢው ማህበረሰብ የመገለል ዕጣ ይደርሰዋል።

መገለሉ በኋላ በሀገር ሽማግሌዎች ለሚጣልበት ቅጣት ዋስ እስከማሳጣት የሚያደርሰው በመሆኑ ሀቅን መናገር ግዴታው ነው።

ተጠርጣሪው ጥፋተኛ መሆኑን ከመነ፣ የሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ዋስ እንዲጠራ ይደረጋል፤ ከዛም በምክርና ተግሳጽ ይለቀቃል።

እንደ ባህል አዋቂው ብርሃኑ ማሬቶ ገለጻ÷ ጥፋተኛው ድጋሜ ሌላ ጥፋት ካጠፋ የሚጠየቀው ዋስ የሆነለት ሰው ነው።

ለሶስተኛ ጊዜ ካጠፋ ግን ዋስ የሆነለት ሰው ዋስትናውን እንዲያወርድ ካደረጉ በኋላ የሀገር ሽማግሌዎች ለዘመናት የቆዩበትን የማሕበረሰብ ሕግ መሰረት አድርገው ጥፋተኛው እንዲቀጣና እንዲታረም ያደርጋሉ።

ይህ የሸካቾዎች የእውነት መንገድ ዘመናዊውን የፍትሕ ሥርዓት በማገዝ ያለው ሚና ከፍ ያለ ነውና ባሕላዊ ክዋኔው ሳይደበዝዝ ለትውልድ እንዲሻገር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

በተስፋዬ ምሬሳ