አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል ቀልጣፍ አገልግሎት መስጠት ያስችላል አሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የሚዛን አማን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል ግንባታ ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡ የአማን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ግንባታ ሥራ በተያዘው መስከረም ወር መጨረሻ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተመላክቷል፡፡
ማዕከሉ በአንድ ጊዜ 32 አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል የመስጠት አቅም ያለው ሲሆን÷ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የተያዘው ራዕይ አንድ አካል ነው። ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የሚዛን አማን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስከረም ወር መገባደጃ ላይ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከተገልጋዮች ዘንድ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን እና እንግልቶችን መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈም ከእጅ ንኪኪ ነጻ የሆነ ዲጂታል አገልግሎትን በማሳለጥ የሚስተዋሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን መቅረፍ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በቀጣይ በክልሉ ክላስተር ከተሞች የማስፋፋቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ በፍሬው ዓለማየሁ