አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያዊያንን ሊያበጣብጥ ይችሉ ይሆናል እንጂ ማሸነፍ አይችሉም አሉ የታሪክ፣ ቅርስ እና ባህል ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር)፡፡
በታሪክ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን በጉልበት ለማሸነፍ በተደጋጋሚ ሞክረው እንዳልተሳካላቸው አንስተው÷ ይህ የሆነውም ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ በዱር በገደሉ የሚታገሉ እና ሞትን የማይፈሩ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ ሁሉም ነገር የሚመሰረተው በታሪክ መሆኑን በመጠቆም÷ ትናንትን ለማወቅ፣ ዛሬን ለመኖር እና ነገር ለማሰብ ታሪክ መሰረት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ታሪክ የሌለው ነገር የለም ያሉት ተመራማሪው÷ የፖለቲካ ታሪክ ብቻ ይዞ መጓዝ ትክክል አለመሆኑንም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በሳይንሱ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗ የተመሰከረላት እና በሃይማኖት መጻሕፍትም በቅድስነቷ በተደጋጋሚ የተጠቀሰች መሆኗን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የታሪክም በተፈጥሮ ሃብትም ባለጸጋ እንደሆነች ጠቁመዋል፡፡
የታሪክ፣ ቅርስ እና ባህል ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ ፡- https://www.youtube.com/watch?v=Irn1LqEpZQM
በብርሃኑ አበራ