አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንድ ወቅት የዝውውር ሒሳቡ ወደ 100 ሚሊየን ዩሮ ከፍ ብሎ የነበረው እንግሊዛዊው ተጫዋች ዴሊ አሊ አሁን ፈላጊ ክለብ ለማግኘት ተቸግሯል፡፡
የ29 ዓመቱ የቶተንሃም የቀድሞ ተጫዋች ዴሊ አሊ በተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ ቢያሳልፍም አሁን እሱን ለማስፈረም ፍላጎት ያለው ክለብ ሊገኝ አልቻለም፡፡
የሕይወት አጋጣሚ ባልጠበቀው መንገድ የወሰደችው ኮከብ እንደዛሬው ብቃቱ ሳይከዳው ብዙ ፈላጊ ክለቦች ነበሩት፡፡
ከዓመት ዓመት ምርጥ ብቃቱን እያጣ የመጣው ዴሊ አሊ በፈረንጆቹ 2023 አስቸጋሪ ጊዜ እያሳለፈ ስለመሆኑ ከጋሪ ኔቪል ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ መናገሩ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ በቃለ ምልልሱ ላይ ከፍተኛ ድብርት ውስጥ ገብቶ እንደነበረ እና የእንቅልፍ መድሃኒት በተደጋጋሚ እንደሚጠቀም ተናግሯል፡፡
ዴሊ አሊ ያሳለፈውን የሕይወት ውጣ ውረድ ከጋሪ ኔቭል ጋር ባደረገው ቆይታ ከተናገረ በኋላም ቢሆን እስካሁን ወደ ቀደመ ብቃቱ መመለስ አልቻለም፡፡
የእንግሊዛዊው ተጫዋች ዴሊ አሊ የእግር ኳስ ሕይወት ዕድገት ከፈረንጆቹ 2015/16 የውድድር ዓመት ጀምሮ እስከ 2019 ድረስ ልዩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በፈረንጆቹ 2015/16 የውድድር ዓመት የተጫዋቶች ማህበር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመባል የተመረጠ ሲሆን ፥ የዝውውር ሒሳቡ ወደ 100 ሚሊየን ዩሮ ከፍ ብሎ ነበር፡፡
ዴሊ አሊ በፈረንጆቹ 2016 የዩሮ ዋንጫ እና በ2018 የሩሲያው የዓለም ዋንጫ ለእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ግልጋሎት መስጠት ችሏል፡፡
በ2019 የውድድር ዓመት ከቶተንሃም ጋር በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ ጥሩ ጊዜን ማሳለፉም ይታወሳል፡፡
ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ ግን ብዙ የተጠበቀው እና ብዙ ክለቦች ይፈልጉት የነበረው ዴሊ አሊ ከቀድሞ ከብቃቱ ጋር መቀጠል አልቻለም፡፡
ዴሊ አሊ በእግር ኳስ ሕይወቱ ለቶተንሃም ሆትስፐር፣ ኤቨርተን፣ ቤሺክታሽ እና ያለፈውን የውድድር ዓመት ደግሞ በጣልያኑ ክለብ ኮሞ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡
ዴሊ አሊ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በጣልያኑ ክለብ ኮሞ ያሳልፍ እንጂ መጫወት የቻለው አንድ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ በአንድ ወቅት ስለ ዴሊ አሊ ብቃት ሲናገሩ ያለውን ምርጥ ብቃት ሙሉ ለሙሉ አላሳየም ብለው ነበር፡፡
ጆዜ በዚህ አላበቁም ለራሱ ለዴሊ አሊ ያለህን ምርጥ ብቃት ተጠቅመህ ያሰብከው ቦታ መድረስ ካልቻልክ ወደፊት ይቆጭሃል፤ ትጸጸታለህም ብለውት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይህ የፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ ምክር አዘል ንግግር ጊዜውን ጠብቆ በዴሌ አሊ ሕይወት ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡
ብዙ የተባለለት እና በአንድ ወቅት የዝውውር ሒሳቡ 100 ሚሊየን ዩሮ ደርሶ የነበረው ኮኮብ ዴሌ አሊ አሁን እሱን የሚያስፈርመው ክለብ አጥቶ ክለብ አልባ ሆኖ ይገኛል፡፡
በአንድ ወቅት ምርጥ ብቃት ላይ የነበረው ተጫዋች ሳይጠበቅ ምርጥ ብቃቱን አጥቶ ከኮንትራት ነጻ የሆነውን ዴሊ አሊን የትኛው ክለብ ያስፈርመዋል የሚለው ይጠበቃል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ