የሀገር ውስጥ ዜና

 ሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

By Mikias Ayele

September 15, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በመጀመሪያ የተወያየው በተሻሻለው የመንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን፥ የአዋጁ መሻሻል የመንግስት ተቋማት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑ በስብሰባው ላይ ተነስቷል፡፡

በተጨማሪም ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው የመንግስት አገልግሎት በመስጠት ለተገልጋዮች ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ እንዲጸድቅ ወደ ክልሉ ምክር ቤት ተመርቷል፡፡

በተመሳሳይ መስተዳድር ምክር ቤቱ የወንዞችና የተፋሰስ ዳርቻዎችን ከብክለት ለመከላከል በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ የተወያየ ሲሆን፥ ህብረተሰቡ በጤናማ፣ ጽዱና ውብ አካባቢ እንዲኖር የሚያስችል አሠራርን ለመዘርጋት ያግዛል ነው የተባለው፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱ በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ ከዛሬ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

የክልሉ ካቢኔ በመቀጠል የአስፈጻሚ ተቋማትን በማዘመን ተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓትን ለመደንገግ በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት በክልሉ ምክር ቤት እንዲጸድቅ መርቷል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይም የተወያየ ሲሆን፥ ረቂቅ አዋጁ አሁን በክልሉ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ያሉበትን ችግሮች እንደሚቀርፍ ታምኖበታል፡፡

በዚህም መሰረት ረቂቅ አዋጁ በክልሉ ምክር ቤት እንዲጸድቅ የተመራ ሲሆን፥ በሌሎች አጀንዳዎች ላይም ውይይት በማድረግ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።