አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት በዛሬው ዕለት የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) ምክር ቤቱ ያደረገውን ግምገማ በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ፥ በክልሉ የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል።
የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ከባለፉት ጊዜያት በእጅጉ እየተሻሻለ መሆኑንና ሕዝቡም የሰላሙ ባለቤትና ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱ በግምገማው ላይ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡
በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉና ሥልጠና እየወሰዱ ወደ ማኅበረሰቡ እየተቀላቀሉ መሆኑን ገልጸው፥ ሕዝባችን ሰላም ማግኘት አለበት በሚል መንፈስ እስካሁን ያጠፉትን ለመካስ ቃል ገብተዋል ነው ያሉት።
የጸጥታ ምክር ቤቱ የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ ያለውን ሥራ መገምገሙን የገለጹት ኃላፊው፥ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ማሳሰቡንም አስረድተዋል።
በክልሉ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለማሸጋገር በቀጣይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል።
የትምህርትና የልማት ሥራዎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ በግምገማው ላይ መነሳቱን አብራርተዋል።
የጸጥታ ምክር ቤቱ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በቀጣይነት እየገመገመ ክልሉ ወደ ተሟላ ሰላም ለማምጣት ሁሉን አቀፍ ሥራ እየሠራ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።