የሀገር ውስጥ ዜና

ሕዝባችን ሰላም ወዳድና ልማት ፈላጊ መሆኑን በተግባር አሳይቷል – አቶ አረጋ ከበደ

By Yonas Getnet

September 16, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕዝባችን ትናንትም ሆነ ዛሬ ሰላም ወዳድ እና ልማት ፈላጊ መሆኑን በተግባር አሳይቷል አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በአማራ ክልል ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ መካሄዱን አንስተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለምረቃ መብቃቱ ለኢትዮጵያ ብሎም ለክልሉ ሕዝብ ታላቅ ትርጉም እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

የሕዳሴ ግድበን ተጨማሪ አቅም በመጠቀም የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡

ሕዳሴ ግድብ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ተግዳሮቶችን ተሻግረን በራሳችን ሃብት፣ ጉልበትና እውቀት የዘመናት የፀና ፍላጎታችንና የዓመታት ልፋታችንን ወደ ውጤት ቀይረን ያረጋገጥንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

አይሳካላቸውም በሚል ሲዘባበቱ የነበሩ የጠላቶቻችንን ትርክት ጥሰንና በጣጥሰን ሕዳሴያችን በጋራ አጠናቅቀን ለድል በቅተናል ያሉት አቶ አረጋ÷ በዚህም ለቀጠናው ሀገራትና ለመላ አፍሪካውያን ዳግም ተምሳሌት መሆን ችለናል ብለዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የዘመኑ ትውልድ የልማት አርበኝነት የተረጋገጠበት እና ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ሁለተኛው የዓድዋ ድል መሆኑን አውስተዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ የሃይል አቅርቦት ፍላጎት በዘላቂነት ከመቅረፍ ባለፈ የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ እንደሚቀይር ጠቁመዋል።

ከግጭት አዙሪት ወጥተን፣ የጋራ ታሪካችን ጠብቀን እና ጸጋዎቻችን በአግባቡ ተጠቅመን ሌላ ድል ለማስመዝገብ በጋራ መቆም ይኖርብናል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የተካሄዱ የድጋፍ ሰልፎች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላት እና ለመላው ሕዝብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!