የሀገር ውስጥ ዜና

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የሐረር ሁለተኛ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀመሩ

By Hailemaryam Tegegn

September 19, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የሐረር ሁለተኛ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀምረዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡

በሐረር የሚገነባው ሞዴል ትምህርት ቤትም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰው፥ በዘመናዊ ትምህርት የታነፀና በእውቀት የበለጸገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የማፍራቱ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

መንግስት በክልሉ ለሚገነባው ሞዴል ትምህርት ቤት ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልጸው፥ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ በጥራትና በፍጥነት ተገንብቶ ይጠናቀቃል ነው ያሉት፡፡

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፥ በክልሉ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው እለት ግንባታው የተጀመረው ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰው፥ ለሞዴል ትምህርት ቤቱ ግንባታ መጀመር ትምህርት ሚኒስቴርን አመስግነዋል።

ትምህርት ቤቱ የክልሉን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ከማሳደግ ባሻገር የአካባቢውን ልማትና እድገት ለማጎልበት የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

በተስፋዬ ሀይሉ