የሀገር ውስጥ ዜና

 ጉባዔው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመሪዎች ዘንድ እውቅና እንዲያገኝ አስችሏል

By Mikias Ayele

September 19, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የተካሄደው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመሪዎች ዘንድ እውቅና እንዲያገኝ አስችሎታል አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፡፡

ሚኒስትሯ ጉባኤውን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፥ ጉባኤው የአፍሪካን የጋራ ድምጽ የያዘውን የአዲስ አበባ ድንጋጌ በማጽደቅ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ተግባራዊ ስታደርገው የቆየችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በድንጋጌው ለአፍሪካ በሞዴልነት እንዲጠቀስ በማድረግ እውቅና ተሰጥቶታል ብለዋል።

በዚህም ለአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት የሚቻልበትን መንገድ ማሳየት መቻሉን ጠቅሰው፥ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ መሆኑን ማስገንዘብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በፖሊሲና በተግባር ያላትን ተሞክሮ በማስመስከር በዘርፉ ያላትን የመሪነት ሚና ለዓለም አሳይታለች ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉባኤዎችን ማስተናገድ እንደምትችልና አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲና የአየር ንብረት ዋና ከተማ መሆኗን ማሳወቅ መቻሉን ነው ያነሱት፡፡

በቀጣይም በፈረንጆቹ 2027 የሚካሄደውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማዘጋጀት ዝግጁ መሆኗን አሳውቃለች ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉባዔው በስኬት እንዲዘጋጅና በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከኢትዮጵያም አልፎ የቀጣናውን የተጎዳ መሬት እንዲያገግም በማስቻል ላበረከቱት አስተዋጽኦ ጉባኤው እውቅና እንደሰጣቸው አንስተዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከሌሎች አህጉር አቀፍ ተነሳሽነቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ እንዲከናወን ከስምምነት መደረሱንም ጠቁመዋል፡፡

በአንዷለም ተስፋዬ