አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 103 ሰልጣኞች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በዚህም 41 አብራሪዎች፣ 343 የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያዎች፣ 524 የበረራ አስተናጋጆች እና 195 በትኬትና በሌሎች ዘርፎች የሰለጠኑ ባለሙያዎች ተመርቀዋል።
ሰልጣኞቹ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች 16 ሀገራት የተወጣጡ መሆናቸው ተገልጿል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቦርድ ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንዳሉት፤ ተመራቂዎች በአዲሱ ጉዞ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በአይበገሬነት በመወጣት ኃላፊነታቸውን በሀገር ወዳድነት ስሜት መወጣት አለባቸው።
የኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 6 አስርት ዓመታት በቀጣናው ግንባር ቀደም ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢንዱስትሪው በቂ የበረራ ባለሙያዎች እያበቃ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች ዛሬ አዲስ ምዕራፍ የከፈታችሁበት ልዩ ቀናችሁ ነው ብለዋል።
የአየር መንገዱ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያዊያንን እና የሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን እያገለገለ የሚገኝ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።
ተቋሙ የደንበኞቹን ፍላጎት በማርካት ተወዳዳሪነቱን ማስጠበቅ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሰማኸኝ ንጋቱ