የሀገር ውስጥ ዜና

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

By abel neway

September 20, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከ700 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ እንዳሉት፤ መንግስት የልማት ጥያቄዎችን በመመለስ የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል።

በዚህም ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመሰረተ ልማት ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት የመስኖ ግድብ እና የአስተዳደር ህንፃ ፕሮጀክቶች በአብነት አንስተዋል።

በተለይም የምግብ ዋስትናን ለሚያረጋግጡ የመስኖ ልማቶች ትኩረት በመስጠት ከዝናብ ጠባቂነት በመላቀቅ በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ ፈዲስ ወረዳ ተገንብቶ ለምረቃ የበቃው የፊና መስኖ ፕሮጀክትም የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ሚስኪ መሐመድ በበኩላቸው የመስኖ ፕሮጀክቱ በዝናብ እጥረት ሳቢያ ለሚቸገረው ህዝብ መፍትሔ በመስጠት ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገር እንደሚያግዘው አስታውቀዋል።

በፈዲስ ወረዳ የተገነባው የፊና የመስኖ ፕሮጀክት ከ210 ሄክታር መሬት በላይ በማልማት 840 አባወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደረግ ተገልጿል።

በምንያህል መለሰ