አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሱዳን በከፍተኛ መጠን ዝናብ እና በጎርፍ አደጋዎች ሳቢያ ከ65 በላይ ሰዎች ህይውት ሲያልፍ፤ ከ14 ሺህ በላይ ቤቶች መውደማቸውን የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል።
የሱዳን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው እለት በሰጠው መግለጫ ነው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በጎርፍ አደጋዎች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ያስታወቀው።
ሚኒስቴሩ በመግለጫውም በጎርፍ አደጋዎቹ እስካሁን ከ65 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን እና ከ14 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን አስታውቋል።
በተጨማሪም 30 ሺህ 400 ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሷል ያለው ሚኒስቴሩ፥ ከ700 በላይ የቀንድ ከብቶችም በጎርፍ አደጋዎቹ መሞታቸውን ገልጿል።
ከ2 ሺህ በላይ በወርቅ ማውጣት ላይ የተሰማሩ ሰዎችም በምስራቅ ጋዳሪፍ ባለው ከፍተኛ የአየር ፀባይ ሳቢያ መውጫ ማጣታቸውንም የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
14 ትምህርት ቤቶችም በጎርፍ አደጋዎቹ ወድመዋል የተባለ ሲሆን፥ ከ1 ሺህ 600 በላይ የመጠጥ ውሃ መሰረተ ልማቶች ደግሞ ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን በሱዳን የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ አስታውቋል።
የአባይ (ናይል) ወንዞች የሚያልፍባቸው የሱዳን ግዛቶች ላይ የጎርፍ አደጋዎቹ መድረሱ የተገለፀ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ጀዚራ፣ ጋዳሪፍ፣ ምእራብ ኮርዶፋን እና ደቡብ ዳርፉር ክልሎች ዋነኛዎቹ ተጎጂዎች መሆናቸውም ታውቋል።
በያዝነው ነሃሴ ወር እንዲሁም በቀጣይ መስከረም ወር በሱዳን ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንደሚጠበቅ ያስታወቀው የሀገሪቱ ሜትሪዮሎጂ ኤጀንሲ፤ ሌሎች አደጋዎች ሊደርሱ እንደሚችሉም አሳስቧል።
ምንጭ፦ aljazeera.com
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።