ስፓርት

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ አዲስ አበባ ገባ

By Mikias Ayele

September 23, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጃፓን ቶኪዮ በተካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ አዲስ አበባ ገብቷል።

ልዑኩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ ሌሎች የስፖርት ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል፡፡

መስከረም 11 ቀን 2018 ዓ.ም ፍጻሜውን ባገኘው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሁለት የብር እና ሁለት ነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን አጠናቅቃለች።

አትሌት ትዕግስት አሰፋ በሴቶች ማራቶን እና አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የብር ሜዳሊያ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች እና ሲምቦ አለማየሁ በሴቶች የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል የነሃስ ሜዳሊያ ለሀገራቸው አስገኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባገኘቸው የሜዳሊያ ብዛት መሰረት አጠቃላይ ከተሳታፊ ሀገራት 22ኛ ደረጃ በመያዝ የቶኪዮ ቆይታዋን ብትቋጭም በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ከ34 ዓመታት በኋላ ያለ ወርቅ ሜዳሊያ የተመለሰችበት ሻምፒዮና ሆኗል፡፡

በወርቅነህ ጋሻሁን