ጤና

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ የወባ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

By Adimasu Aragawu

September 23, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ የወባ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀምሯል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የመጀመሪያውን የወባ መከላከያ ክትባት በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።

አቶ ሳሙኤል በዚህ ወቅት እንደ ሀገር ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው÷ በክልሉ በመደበኛነት የወባ በሽታን ለመከላከል ከሚተገበሩ ስራዎች በተጓዳኝ ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ከ2 ዓመት በታች እና ከ6 ወራት በላይ ላሉ ህጻናት የሚሰጠው የወባ መከላከያ ክትባት መጀመሩን ጠቅሰው÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የክትባት ዓይነቶች ቁጥር ወደ 14 ከፍ እንደሚያደርገው አመላክተዋል።

የወባ በሽታ በህጻናት ህይወት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ያሉት ኃላፊው÷ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ማዳፈንና ማፋሰስ፣ የአጎበር አጠቃቀምን ማሳደግ፣ የኬሚካል ርጭት እና ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን ማጠናከር በሽታውን መከላከል ያስችላል ብለዋል።

የወባ መከላከያ ክትባት መጀመሩ የሕብረተሰቡን ጤና በማሻሻል ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለውና በሽታውን ለመከላከል የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር ተገቢ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር ከተመረጡ አካባቢዎች የወባ በሽታ ጫና ያለበት የቁሊቶ ከተማ መሆኑን አንስተው÷ በሙከራ ደረጃ እየተሰጠ ያለው ክትባት ለክልሉ ብሎም ለቁሊቶ ከተማ ሕዝብ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook WMCC TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!