የሀገር ውስጥ ዜና

የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል – ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

By Adimasu Aragawu

September 23, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ መድሃኒቶችንና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል አለ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር።

የኢትዮጵያ መድሃኒትና ሕክምና መገልገያዎች አምራች ዘርፍ ማህበር 22ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ተካሂዷል።

በጉባዔው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ፣ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳንዔል ዋቅቶሌ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ አሁን ላይ በመድሃኒት እና ሕክምና መገልገያዎች አምራች ዘርፍ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወነ ሥራም የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በዚህም ለጤና ዘርፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል ያሉት አቶ መላኩ÷ በዘርፉ በተኪ ምርቶች ላይ ለሚሰማሩ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው፥ በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ለማሻሻልና ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በመከላከልና አክሞ ማዳን ላይ መሰረት ያደረገውን የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው÷ ማህበሩ ጥራትና እሴት የተጨመረባቸውን የሕክምና መገልገያዎች የማምረቱን ሒደት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ዶ/ር ዳንኤል ዋቅቶሌ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ይነሱ የነበሩ ተግዳሮቶችን ከመቀነስ አንጻር ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

ይህም ከውጪ ይገቡ የነበሩ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ነው ያስረዱት።

የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከርም የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ አሠራርን ማቀላጠፍ እና የገበያ ትስስርን ማስፋት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በመላኩ ገድፍ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!