አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የባሕር ላይና ዳርቻዎች ጥበቃ ፖሊስ (ኮስታል ጋርድ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ንጋት ሐይቅ ላይ ሥራ ጀምሯል አሉ፡፡
ኮሚሽነር ጀነራሉ እንዳሉት÷ ወንጀልን አስቀድሞ መከላከል እና ሲፈጸም በብቃት መመርመር የሚያስችል ዘመናዊ የፖሊስ ተቋም እየተገነባ ነው።
ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደሕንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሥራውን በአግባቡ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል የውሃ አካላትን ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል የባሕር ላይና ዳርቻዎች ጥበቃ (ኮስታል ጋርድ) የተሰኘ የፖሊስ ክፍል መደራጀቱን ጠቅሰው፤ የጥበቃ ክፍሉ በሕዳሴ ግድብ ንጋት ሐይቅ ሥራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
ኮስታል ጋርድ ዘመናዊ የሞተር ጀልባዎችን የታጠቀ መሆኑን በማንሳት፤ ጀልባዎቹ በሐይቆችና ሌሎች የውሃ አካላት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የደሕንነት ሥጋቶችን መከላከልና በብቃት ምላሽ መስጠት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮስታል ጋርድ አባላት በዘርፉ በቂ ስልጠና ያገኙና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ዘመናዊ የሞተር ጀልባዎቹ የክትትል ካሜራዎች፣ የላቀ የመገናኛ ዘዴዎች እና የራዳር ሲስተም የተገጠመላቸው መሆናቸውን ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል፡፡
ጀልባዎቹ በውሃ አካላት ላይ የሚፈጠሩ ማናቸውንም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችና የደሕንነት ስጋቶችን በብቃት መቆጣጠር ያስችላሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡