የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ የስፖርት ሜዳ አርቴፊሻል ሳር ለማልበስ የሚያስችል ስምምነት ተደረገ

By Yonas Getnet

September 24, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የስፖርት ሜዳዎችን አርቴፊሻል ሳር ለማልበስ የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል።

በስምምነት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጂራ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የስምምነት ፊርማውን የፈረሙት ታን ኢንጂነሪንግ እና መቀመጫውን በቻይና ያደረገው ሲቲ ግሪን ናቸው።

ሲቲ ግሪን ለእንግሊዙ ቡድን ቶተንሃም ሳር አቅራቢ ኩባንያ መሆኑ ተገልጿል።

በስምምነቱ መሰረት ሲቲ ግሪን በኢትዮጵያ ያለውን የአርቲፊሻል ሳር ግንዛቤ ለማሳደግ ባለሙያዎችን ወደ እንግሊዝ በመውሰድ ልምድ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ በተወካዮቹ አማካኝነት ይፋ አድርጓል።

የታን ኢንጂነሪንግ ስራ አስኪያጅ ፉአድ ኢብራሂም እንዳሉት፤ ለኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ ሰው ሰራሽ ሳሮችን ለማቅረብ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

ከዚህ ቀደም የድሬዳዋ እና ሃላባ ስታዲየሞችን የመጫዎቻ ሜዳ የሰው ሰራሽ ሳር በማንጠፍ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ሰርተፊኬት ባለቤት ማድረጉን አስታውሰው፤ ተቋሙ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት በአዲስ አበባ ቢሮ መክፈቱን ጠቁመዋል።

በእንዳልካቸው ወዳጄ