የሀገር ውስጥ ዜና

የዣውሻ ሳኣ ጉልአ ተራራን ለቱሪዝም መስህብነት የማልማት ሥራ…

By Hailemaryam Tegegn

September 25, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን የሚገኘውን የዣውሻ ሳኣ ጉልአ ተራራን ለቱሪዝም መስህብነት የማልማት ሥራ ሊከናወን ነው፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) እና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የዣውሻ ሳኣ ጉልአ ተራራን ጎብኝተዋል፡፡ ‌‎ ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በዞኑ ኦይዳ ወረዳ በሚገኘው ታሪካዊውና ተፈጥሯዊው የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ታቅዷል፡፡

በተራራው አናት ላይ ሰገነት እንደሚገነባ ጠቁመው፥ በጎፋ ልማት ማህበር ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የቱሪስት መዳረሻውን የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበው፥ በተለይም በጎፋ ጋዜና ኦይዳ ዮኦ ማስቃላ የዘመን መለወጫ በዓል ማግስት የሚጎበኝ የቱሪስት መስህብ ሥፍራ ይሆናል ብለዋል። ‎ ‎የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር) በበኩላቸው፥ የዣውሻ ሳኣ ጉልአ ተራራን የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ ለማልማት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ ‎ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ ከባሕር ጠለል በላይ 1ሺህ 800 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው ‎የዣውሻ ሳኣ ጉልአ ተራራ 202 ሄክታር ይሸፍናል፡፡