አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደ ዓድዋ ድል አይነት ለትውልድ በሚተላለፉ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሊኖር አይገባም አሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ም/መሪ አቶ ዮሐንስ መኮንን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ ይህ ትውልድ ሁሉንም ጫና አምክኖ የዘመናት ሕልምና ቁጭት የነበረውን ሕዳሴ ግድብ እውን አድርጓል፡፡
ሕዳሴ ግድብ ባለፉት 14 ዓመታት ሁሉም የማሕበረሰብ ክፍል እንዲሁም የተለያየ ዝንባሌና አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች በአንድነት ያሳኩት የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ሃውልት ነው ብለዋል።
በአንጻሩ የውጭ ኃይሎች መንግስት ላይ ቅሬታ ያላቸው አኩራፊ ኃይሎችን በማስተባበር በአቅርቦት፣ በኃሳብና በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ መሰል ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በዚህ ዘመን ያሉ የኢትዮጵያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግድቡን የጋራ ጉዳይ እና አጀንዳ በማድረግ በአንድነት መስራታቸው የሚያስመሰግን ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በርካታ ኢንዱስትሪዎችን ለማንቀሳቀስ ዕድል እንደሚፈጥርም አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ የብሔራዊ ጥቅሞቻችን መገለጫ የሆኑ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንደሚጠበቁ ጠቁመው ÷ ለአብነትም የባሕር በርና የሀገራዊ ምክክርን በስኬት ማጠናቀቅ መቻልን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሰብሳቢ ራሄል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ከሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ከግብጽ እና ሱዳን በኩል ከባድ የሆነ ጫና ሲፈጠር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በወቅቱ ግድቡን አትሰሩም የሚል ጫና ብቻ ሳይሆን ከዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት የላችሁም የሚል ግፊት እና ጫና ነበር ፤ ይህም እስከ አሜሪካ የደረሰ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የዚህ ትውልድ ታሪክ መጻፊያ መሆኑን አንስተው ÷ እንደ ዓድዋ ድል ለትውልድ በሚተላለፉ ጉዳዮች ላይ ምንም ልዩነት ሊኖር አይገባም ፤ ምክንያቱም ሁላችንም ያለን አንድ ሀገር ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በውጭ ሀገራት ሲደረጉ የነበሩ ጫናዎችን በዚህ ልክ መመከት ከቻልን በሀገር ውስጥ ያሉ ችግሮችንም በመነጋገርና በመወያየት ልዩነቶችን ከጦር መሳሪያ ይልቅ በንግግር መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!