የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በቀጣይ በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ላይ በትኩረት ትሰራለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

September 26, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣይነት በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ በትኩረት ትሰራለች አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የኒውክሌር ልማትን አስመልክቶ የሁለትዮሽ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

በውይይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ የንቁ ወጣቶች መገኛ መሆኗን ጠቅሰው፥ በወሳኝ የእድገት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከተሞች እየዘመኑ እንደሚገኙና ኢንዱስትሪዎች በማደግ ላይ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓለም ላይ ፈጣን እድገት እያሳዩ ካሉ የሀገራት ኢኮኖሚ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ኃይል ዘርፍ ምሳሌ ሆና መቆየቷን ጠቅሰው፥ ለአብነትም በቅርቡ ተጠናቅቆ ለምረቃ የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዘርፉ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት፡፡

ራዕያችን ከዛሬ የተሻገረ በመሆኑ የተለያዩ የልማት አማራጮችን ተግባራዊ እናደርጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በቀጣይነት በኒውክለር ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፥ ለህክምና፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለውሃ አስተዳደር እንዲሁም ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ