ምስራቅ ዕዝ የጽንፈኛ ቡድኑን እንቅስቃሴ ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ ሰላም እያጸና ነው – ጀነራል አበባው ታደሰ

By Abiy Getahun

September 26, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምስራቅ ዕዝ የጽንፈኛ ቡድኑን እንቅስቃሴ ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ ሰላም እያጸና ነው አሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም እና የአማራ ክልል የፀጥታ ካውንስል ሰብሳቢ ጀነራል አበባው ታደሰ።

የምስራቅ ዕዝን የተልእኮ አፈጻጸምና በአካባቢው የተፈጠረውን ሰላም በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት ጀነራል አበባው ታደሰ፤ የዕዙ አመራርና ሰራዊቱ ህገ መንግስታዊና ሀገራዊ ተልእኮውን በፅኑ የሀገር ፍቅርና በጥብቅ ዲሲፕሊን እየፈፀመ ይገኛል ብለዋል።

የዕዙ አባላት በላቀ የግዳጅ አፈፃፀም የክልሉ ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ በመስራት ሀገራዊ ተልእኳቸውን በላቀ ብቃት እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተልዕኮ መፈፀም ባለፈ የክልሉን የጸጥታ ሃይል እንደገና በማደራጀት፣ በማሰልጠንና በማብቃት የተጠናከረ የጸጥታ መዋቅር እንዲኖር ተደርጓል ነው ያሉት።

በዚህም መሰረት የምስራቅ ዕዝ በጎጃምና ደቡብ ጎንደር ዞኖች የጽንፈኛ ቡድኑን እንቅስቃሴ ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ሰላም እያጸና መሆኑን ገልጸዋል።

የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ዓላማ ተቀብሎ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በተወሰደበት ጠንካራ እርምጃ አሁን ላይ ተስፋ በመቁረጥ ላይ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በጥፋት ቡድኑ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ፍቅርንና ህዝባዊነትን በመላበስ በጥብቅ ዲሲፕሊን በጀግንነትና በዓላማ ቁርጠኝነት የሀገሩን ክብርና ሉአላዊነት ማስጠበቁን ይቀጥላል ብለዋል።

በየደረጃው የሠራዊቱ አመራሮች የላቀ የመምራት ብቃት እንዳላቸው አንስተው፤ በዚሁ መልኩ መቀጠል አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል።