አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የመስቀል ደመራ በዓል ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያሳይ ድንቅ ሀይማኖታዊ በዓል ነው አሉ፡፡
የ2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።
ሚኒስትሯ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ እንደ ችቦ እንጨት የብዙ ባህሎች፣ ውብ እሴቶች፣ ብዝሃ ሀብት እና ታሪክ ያላት ሀገር ናት ብለዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል አንዱ የመስቀል ደመራ በዓል መሆኑን ጠቅሰው፤ መስቀል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስ የተመዘገበ የዓለም ሀብት መሆኑን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያን ብዝሃ ባህልና እሴት የሚያፀባርቀው የመስቀል በዓል ኢትዮጵያውያንን በጋራ የሚያስተሳስር በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ በአጋጣሚ ወይ በድንገት የመጣ አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ፤ መስቀል በተለያየ ሁነት በሁሉም አካባቢዎች ዘንድ መከበሩ ኢትዮጵያውያን የቆየ የጋራ ታሪክ እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህም በዓሉን የህብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ ያደርገዋል በማለት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የዳበረ እና በትውልድ ቅብብሎሽ የጎለበተ እምቅ የባህል ሀብት ያላት ውብ እና ታሪካዊ ምድር ናት ብለዋል።
የዘንደሮው የመስቀል ደመራ በዓል ኢትዮጵያ ውጣ ውረዶችን አልፋ የማንሰራራት ዘመን ላይ በምትገኝበት ወቅት እየተከበረ መሆኑን አንስተው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንዳሳካነው በጋራ የምናሳከቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ ሲሉ ገልጸዋል።
የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ የጋራ ጥረት እና ድካም ይፈልጋል ብለዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ