የሀገር ውስጥ ዜና

ፍጹምና ዘላቂ ሰላም የምንሻ ከሆነ ይቅርታን፣ አንድነትን፣ ፍትህን ማረጋገጥ ይገባል – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

By Mikias Ayele

September 26, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፍጹም እና ዘላቂ ሰላምን የምንሻ ከሆነ ይቅርታን እና ዕርቅን፣ እኩልነትን እና አንድነትን፣ ፍትህን እና ርትዕን ማረጋገጥ ይገባል አሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት።

የ2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ እንኳን ለ2018 ዓ.ም በዓለ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

በእግዚአብሔር ኃይል በጢሰ እጣን አመልካችነት ከተቀበረበት ጉድጓድ የወጣው መስቀል እስከዛሬ ድረስ የእውነት መስካሪ እና የድኅነት ምልክት ሆኖ ቀጥሏል ነው ያሉት።

ዛሬ ላይ ሕገ እግዚአብሔር በድፍረት ይጣሳል፣ የዚህ ውጤትም ዓለምን በአጠቃላይ በመኖር እና ባለመኖር መካከል እየከተተ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ፍጹም እና ዘላቂ ሰላምን የምንሻ ከሆነ ይቅርታን እና ዕርቅን፣ እኩልነትን እና አንድነትን፣ ፍትህን እና ርትዕን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዘንድሮው የመስቀል በዓል አከባበር እግዚአብሔር የሰጠን የውሃ ጸጋችን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም በአንድነት ባካሄድነው ተግባር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድባችንን አጠናቀን ባስመረቅንበት ማግስት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ይህ ክስተት ለሀገራችን የዳግም ልደትን ያበሰረ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም ያሉት ብጹዕነታቸው፤ በግድቡ ግንባታ ስራ ላይ ታሪካዊ አሻራቻውን ያሳረፉትንም ሁሉ ማመስገን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በቀጣይ ሀገራችን ልትሰራቸው በዕቅድ የያዘቻቸውን ታላላቅ ስራዎች በፍጥነት እና በጥራት ተሰርተው ለሕዝባችን ጥቅም እንዲውሉ ሁላችንም መረባረብ ይኖርብናልም ነው ያሉት።

ታላላቅ እና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሁም ችግር አስወጋጅ ስራዎች እውን ሊሆኑ የሚችሉት ሕዝቡ በአንድነት እና በሕብረት ሲሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ በግድቡ የታየው ትብብር እና ተነሳሽነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

አለመግባባቶችን በዕርቅ እና በይቅርታ በማለፍ እኩልነትን፣ ፍትህን እና ርትዕን በማረጋገጥ እንዲሁም ለሰላም መስፈን ረዥም ጉዞ በመሄድ ሕዝቡን ወደ አንድነት ማምጣት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የመስቀሉ መልዕክት የሰው ልጅን ሁሉ በሰላም፣ በሕይወት፣ በእኩልነት፣ በአንድነት ማኖር መሆኑን በመገንዘብ ከመጠፋፋት ይልቅ በጋራ መልማትን ምርጫ ማድረግ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

በዮናስ ጌትነት