ቴክ

የኢትዮ-ቻይና የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ ትብብር

By Mikias Ayele

September 26, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቻይና በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ ትብብራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በቻይና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ይን ሔጁን ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ሀገራቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው።

ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ ሰላም፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ግብርና እና ምርምር የትብብሮቻቸው የትኩረት ማዕከሎች መሆናቸውንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ በርካታ ለውጦችን ያስመዘገበች መሆኑን ጠቅሰው፤ በቴክኖሎጂ እና ሌሎች ዘርፎች ከቻይና ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ይን ሔጁን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሰጠችው ትኩረት የሚደነቅ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅት ቻይና እና ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ የዓለም ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም መሆናቸውን አንስተዋል።

ይህን ፈጣንና ሁለንተናዊ እድገት አስጠብቆ ለማስቀጠል ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።