አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ በቴክኖሎጂ፣ ሳይንስ እና ፈጠራ ዘርፎች ላይ የሚሰራው “አንሶ አፍሪካ” የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ልሕቀት ማዕከል በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተከፍቷል።
በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ወቅት እንደተገለጸው፥ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ የልህቀት ማዕከሉ በአፍሪካ ደረጃ በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራትን ያስተባብራል።
የልህቀት ማዕከሉ በዘርፉ ያሉ እውቀትና ሃብቶችን ከመደገፍ ባሻገር በአህጉሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ምሁራኖችና ኢንዱስትሪዎች በጋራ የሚሰሩበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ (ዶ/ር)፥ የማዕከሉ እውን መሆን ኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልሕቀት ማዕከል ለመሆን የጀመረችውን ጉዞ ያፋጥናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት፣ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት ሰፊ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ባይሳ ለታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የልህቀት ማዕከሉ የትምህርት ተቋሞቻቸን ወደ ዓለም አቀፍ ተቋምነትና የምርምር ማዕከልነት የሚያደርጉትን ሽግግር ያግዛል ነው ያሉት፡፡
ማዕከሉ በአህጉሪቱ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሃሳቦችን ወደ ተግባር ለመቀየርና እውቀትና ሃብታቸውን ደምረው በስራቸው ላይ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባሻገር ኢንዱስትሪዎቻችን የተሻለ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለዓለም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ብለዋል፡፡
አንሶ በቻይና መንግስት ድጋፍ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርን ለመፍጠር እንዲሁም ሳይንስና ፈጠራ ለማበረታታት የሚሰራ ድርጅት ነው።
በመራኦል ከድር