የሀገር ውስጥ ዜና

“ጋሪ ዎሮ” የዘመን መለወጫ በዓል ማሕበራዊ መስተጋብር የሚጠናከርበት ነው – አቶ አሻድሊ

By abel neway

September 27, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቦሮ ሽናሻ “ጋሪ ዎሮ” የዘመን መለወጫ በዓል ይቅር ባይነትና ማሕበራዊ መስተጋብር የሚጠናከርበት ነው አሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን።

የቦሮ ሽናሻ የዘመን መለወጫ በዓል “ጋሪ ዎሮ” በአሶሳ ከተማ በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።

አቶ አሻድሊ ሃሰን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የቦሮ ሽናሻ የዘመን መለወጫ “ጋሪ ዎሮ” በዓል የይቅር ባይነት ፣ የአንድነትና የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ሥነ ሥርዓት የሚከወንበት ነው።

በዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ማሕበራዊ መስተጋብር የሚጠናከርበትና ባሕላዊ መገለጫዎቹ የሚተዋወቁበት እንደሆነም ገልጸዋል።

“ጋሪ ዎሮ” በአደባባይ የሚከበር በመሆኑ የክልሉ መንግስት የዘመን መለወጫ ማክበሪያ የሚሆን ቦታ “ጋሪ ጀባ” በአሶሳ ከተማ እንዲመቻች መወሰኑን ጠቅሰዋል።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነፊሳ አልማሕዲ በበኩላቸው ÷ የቦሮ ሽናሻ “ጋሪ ዎሮ” የዘመን መለወጫ በዓል ቂም እና ጥላቻ በፍቅር የሚሸነፉበት ትልቅ እሴት መሆኑን ተናግረዋል።

የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራራቀ የሚቀራረብበት፣ የአብሮነት እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት በዓል እንደሆነም አንስተዋል።