የሀገር ውስጥ ዜና

የመስቀል ደመራ የኢትዮጵያውያን አንድነት ደምቆ የሚታይበት ልዩ የአደባባይ በዓል ነው – የተለያዩ ሀገራት ዜጎች

By abel neway

September 27, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመስቀል ደመራ የኢትዮጵያውያን አንድነት ደምቆ የሚታይበት ልዩ የአደባባይ በዓል ነው አሉ በበዓሉ አከባበር ላይ የታደሙ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ትናንት በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል።

የመስቀል ደመራ በዓል በዓለም የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መመዝገቡን ተከትሎ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ሆኗል።

በዚህም በየዓመቱ የተለያዩ ሀገራት ቱሪስቶች የደመራና የመስቀል በዓላትን ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ።

የዘንድሮው የደመራ በዓልን ለመታደም መስቀል አደባባይ ከተገኙት የውጭ ሀገራት ዜጎች መካከል ኬንያዊው ዊክሊቭ ኦሎ ስፔናዊቷ ቪኪ አንቶኒዮ እንዲሁም አርሜኒያዊው ሳርጊስ ሀሩዩኒያ ይገኙበታል።

እነርሱ እንደሚሉት የኢትዮጵያውያን የመስቀል ደመራ አከባበር ከሌሎች ሀገራት የተለየና የደመቀ ነው።

ኬንያዊው ዊክሊቭ ኦሎ የደመራ በዓል ላይ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችን በአንድነት ማየት የተለየ እንደሚያደርገው ገልጾ ÷ በሌሎች ሀገራት እንዲህ አይነት ብዛት ያለው ሕዝብ አንድ ላይ ተሰባስቦ ማክበሩ የተለመደ አለመሆኑን ተናግረዋል።

የሕዝቡን የአንድነት መንፈስ አድንቀው በሀገራቸውም ሕዝቡ በአንድነት መንፈስ ተሰባስቦ በዓል የሚያከብርበት ሁኔታ እንዲኖር ተመኝተዋል።

ስፔናዊቷ ቪኪ አንቶኒዮ እንዲሁም አርሜኒያዊው ሳርጊስ ሀሩዩኒያ የኢትዮጵያ ባሕል የሚናፈቅና ልዩ ስሜት የሚሰጥ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ሀገራትን የማየት አጋጣሚ እንደነበራቸውና የኢትዮጵያ የአደባባይ በዓል አከባበር ግን ከሁሉም እንደተለየባቸው የሚናገሩት ደግሞ ጀርመናዊው ኡሊ ባጅ እና እንግሊዛዊው ዊሊያም ስሚዝ ናቸው።

ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን የመሰረተ ልማት ዕድገት ያደነቁት አስተያየት ሰጪዎቹ ቱሪስቶች ባላቸው ጊዜ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጠይቀዋል።