አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ከኒውክሌር ፕሮግራም ጋር በተያያዘ በኢራን ላይ በድጋሚ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ማዕቀብ ጥሏል፡፡
ምክር ቤቱ በፈረንጆቹ 2015 ስምምነት መሠረት በኢራን ላይ ተነስቶ የነበረው ማዕቀብ ነው በድጋሚ እንዲጣል የወሰነው፡፡
ውሳኔው የተላለፈውም ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ኢራን ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር ቁርጠኛ አይደለችም በሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው፡፡
በአንጻሩ ቻይና እና ሩሲያ በኢራን ላይ የሚጣለው ማዕቀብ ለስድስት ወራት እንዲዘገይ መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጂ በኢራን ላይ ማዕቀብ ለመጣል የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በሌሎቹ የጸጥታው ም/ቤት አባላት አብላጫ ድምጽ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡
የኢራን ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ÷ በቴህራን ላይ በድጋሚ የተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ተቀባይነት የሌለው፣ ሕገ ወጥና ኢፍትሃዊ ነው ሲሉ አውግዘዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የማበልጸግ ፍላጎት እንደሌላትና በጉዳዩ ላይም አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ ኢራን በዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የሚገኙ አምባሳደሮቿን ለምክክር መጥራቷ ተጠቅሷል፡፡
በቴህራን ላይ በድጋሚ የተጣለው ሁሉን አቀፍ ማዕቀብ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡
በአቤል ነዋይ