አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደመራ እና መስቀል በዓል በድምቀት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርባለች፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ÷ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ አደረጃጀት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ያዋቀረችው ልዩ የበዓል ዝግጅት ኮሚቴ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማትና ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተቀናጅቶ በጋራ በመስራቱ በዓሉ በድምቀትና መንፈሳዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ተከብሯል ነው ያሉት፡፡
በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነው ÷ ለቅን አገልጋዮችና መላው ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ከበዓሉ በፊት ልዩ ዝግጅት በማድረግና ለረጅም ቀናት የሌሊት ቁሩና የቀን ሀሩር ሳይበግራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌዴራል፣ የሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የፀጥታና መስተዳድር አካላት እንዲሁም ለመላው ኦርቶዶክሳዊያንና ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የበዓሉን ዝግጅት ሙሉ ወጪ በመሸፈን እና ሌሎች የሥራ ድጋፎችና ትብብሮች በማድረግ ከፍተኛውን ሚና ለተጫወቱት ከንቲባ አዳነች አበቤ እና የካቢኔ አባላቶቻቸውንም አመስግነዋል፡፡
በሌላ በኩል በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሕገ ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ ተገቢው የሕግ እርምት እንዲሰጥ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ሰመረትም በቅርቡ ስዕለ ቅድስት ድንግል ማርያምን በመቅደድ ሕገ ወጥና አስነዋሪ ተግባር የፈጸመችውን ግለሰብ በሕግ ቁጥጥር ስር በማዋል ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለተሰጠው ፈጣን ምላሽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይ እንዲህ አይነቱ ሕግን የማስከበር እና ሕገ ወጥ ግለሰቦችን በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡