የሀገር ውስጥ ዜና

የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለዜጎች የሚሰጠውን ሰው ተኮር አገልግሎት የሚያሻሽል ነው – አቶ አረጋ ከበደ

By Adimasu Aragawu

September 28, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥት ለዜጎች የሚሰጠውን ሰው ተኮር አገልግሎት በማሻሻል የመንግሥትና ሕዝብ ግንኙነት በእጅጉ የሚያሻሽል ነው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና ሌሎች የፌዴራልና ክልል ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

አቶ አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት÷ መንግሥት ለሕዝብ አንገብጋቢ የመልካም አስተዳደር ችግር ብሎ ከለያቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ማዕከሉ ይህንን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ዘመኑን የዋጀ በቴክኖሎጂና የዓለም ማኅበረሰብ ልምድ በመውሰድ የሕዝቡን የአገልግሎት ዘርፎች ወደ አንድ ማዕከል በማምጣትና ቅልጥፍናን በማሳለጥ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ መቋቋሙን ተናግረዋል።

የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ከባሕር ዳር ቀጥሎ በጎንደር እና ደሴ ከተሞች አገልግሎቱን ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አገልግሎት መጀመሩ ለሕዝቡ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸውን አንስተው÷ መንግሥት ለዜጎች የሚሰጠውን ሰው ተኮር አገልግሎት በማሻሻል የመንግሥትና ሕዝብ ግንኙነት በእጅጉ የሚያሻሽል እንዲሁም እርካታና ቅቡልነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ አመልክተዋል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!