የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በሚሰሩ የልማት ሥራዎች ሁሉ ኪነ ጥበብ አበይት የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ እየተተገበረ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Melaku Gedif

September 28, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚሰሩ የልማት ሥራዎች ሁሉ ኪነ ጥበብ አበይት የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ እየተተገበረ ነው አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባ አዳነች በአይነቱ የመጀመሪያና እጅግ ዘመናዊ የሆነው የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት መርቀን ስራ አስጀምረናል ብለዋል።

በዚህ ወቅትም የከተማችን አስተዳደር በሚሰራቸው የልማት ሥራዎች ሁሉ ኪነ ጥበብን አበይት የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ እየተገበረ እንደሚገኝ ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነባሮቹን በማደስ ዘመናዊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በማድረግ እንዲሁም አዳዲስ እና ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው የቴአትርና የሲኒማ ኮምፕሌክሶች ገንብተን ለኪነ ጥበብ ዘርፉ እድገት አስተዋፆ እያበረከትን እንገኛለን ነው ያሉት።

ዛሬ የተመረቀው የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ ባለ14 ወለል ህንፃ ፣2 ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶችን፣የቴአትር አዳራሽ ፣3 የተለያዩ አዳራሾችን ፣ ሆቴል እና ሬስቶራንት ዘመናዊ ካፍቴሪያዎችን እና የፓርኪንግ አገልግሎትን ይዟል ።

የጥበብ ስራ በአዳራሽ ብቻ የተወሰነ ባለመሆኑ እና ወደ ማህበረሰቡ ቀረብ እንዲል በከተማችን በተገበርነው ሁለንተናዊ ለውጥ የተለያዩ የውጭ የኪነ ጥበብ ስራ የሚከወንባቸው ከ160 በላይ አንፊ ቴአትርና ፕላዛዎችን ገንብተን ለአገልግሎት አውለናል ብለዋል።

የኪነ ጥበብ ዘርፉ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ የውስጥ ቁጭትን በመፍጠር ትውልድን በመልካም ሥራ እናንጽ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡