አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የተመለከቱ በርካታ ምዕራፎች አካቷል አለ የትምህርት ሚኒስቴር።
በሚኒስቴሩ የማሕበራዊ ሳይንስ ሥርዓተ ትምህርት ማበልጸጊያ መሪ ስራ አስፈጻሚ ኡመር ኢማም የግድቡ መመረቅ የታሪክ ትምህርትን ከፖለቲካዊ ትርክት ወደ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ይዘት እንዲቀየር አድርጎታል ብለዋል፡፡
አዲሱ ሥርዓተ ትምህርትም ግድቡን የተመለከቱ በርካታ ምዕራፎች እና ንዑስ ምዕራፎችን ማካተቱን አመላክተዋል፡፡
የሕዳሴ ግድቡ አጠቃላይ ሁኔታ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተት ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ እና የሀገር ፍቅር የሚያሰርጽ መሆኑን ጠቁመው÷ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ትውልድን ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው አንስተዋል፡፡
ስለግድቡ አጠቃላይ ሁኔታ ህጻናት እና ታዳጊዎች መማራቸው ብሔራዊ ኩራት እና ለተጨማሪ ስራ ተነሳሽነት የሚፈጥር እንዳለውም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስሟ ሲጠራ ሰንደቅ ዓለማዋ እና ብሔራዊ መዝሙሯ አብረው እንደሚስተጋቡት ሁሉ ሕዳሴ ግድቡም ብሔራዊ አርማ እንዲሆን ለማድረግ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በጸጋዬ ንጉስ