የሀገር ውስጥ ዜና

ዳኞች ሞዴል የፍትህ ተቋም ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት አካል መሆን ይገባቸዋል

By Adimasu Aragawu

September 30, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዳኞች ሞዴል የፍትህ ተቋም ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት አካል መሆን ይገባቸዋል አሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ።

ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚካሄደውና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያዘጋጀው የዳኞች ጉባኤ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ የተጀመረ ሲሆን÷ ከ 2 ሺህ 200 በላይ ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎችና የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ተሳትፈዋል።

በመክፈቻው ላይ የተገኙት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ÷ ዳኞች በሐሳቦች፣ እቅዶች፣ ሕጎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም በለውጥ አሠራሮች ላይ ተግባብተውና ወጥ አቋም ይዘው የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሞዴል የፍትህ ተቋም ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት አካል መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው በበኩላቸው÷ ጉባኤው የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት በማላቅ የሕዝብ አመኔታን መፍጠርና ትክክለኛ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ማዕከላት እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቶች የፍትህ አስኳል እንደመሆናቸው መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን በማስፈንና የተረጋጋ ማኅበረሰብ በመገንባት ሰላምና ልማት የሰፈነበት ሀገር ለማቆም ያላቸውን ሚና መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።

ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ብቁና ቅቡልነት ያላቸው ፍርድ ቤቶችን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አንስተው÷ የለውጥ ሥራዎችን በመምራት፣ ብቁ የሰው ኃይል በመገንባትና አገልግሎቱን በማዘመን የፍርድ ተደራሽነትን ማስፈን የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ነጻነትን የሚገዳደሩ ተግዳሮቶችን ከመቅረፍ በተጨማሪ ዘመናዊ ተቋማትንና አሰራሮችን በማረጋገጥ ፍትህን ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ማኅበረሰቡ እንዲያግዝ ጥሪ ቀርቧል።

በዳኞች ጉባኤ ልምድ ባላቸውና በዘርፉ ምሁራን ጥልቅ ውይይቶችና ስልጠናዎች የሚሰጡ ሲሆን÷ ዳኞች እውቀትና ልምድ የሚያገኙበት ይሆናልም ተብሏል።

በደሳለኝ ቢራራ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!