የሀገር ውስጥ ዜና

በሶማሌ ክልል ያለውን መነቃቃት የሚገልጽ የሥራ እድገት ተመልክተናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By abel neway

October 01, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ባደረግነው ጉብኝት የተመለከትነው የሥራ እድገት በጂግጂጋና በመላው ክልሉ ያለውን መነቃቃት የሚገልጽ ነው አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ዛሬ የተመለከትናት ጅግጅጋ ባለፈው ጥር ከተመለከትናት ይዞታዋ በሚታይ መልክ የተቀየረች ናት ብለዋል።

በመላው ከተማዋ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰው፥ የከተማዋ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች በሁሉም አካባቢ የመኖሪያ ሁኔታን በግልጽ እያሻሻሉ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የከተማ ማዕከሎቻችንን ስናዘምን የምንገነባው ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም መሠረት እያኖርን መሆኑን መገንዘብ ይገባናልም ነው ያሉት፡፡

ርዕያችን እንደ ኢትዮጵያዊ እና አፍሪካዊ ጠቃሚ በሆኑልን ጉዳዮች ላይ የተተከለ መሆኑን ማስታወስ ይገባናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ መንፈስ የሶማሌ ክልል በቱሪዝም አዳዲስ እድሎችን እየከፈተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ መጠናቀቂያ ምዕራፍ በደረሰው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለምስራቁ የሀገራችን ክፍል አዲስ ዋጋ የጨመረ እድል እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡