አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) የፓኪስታንን እና የኢትዮጵያን ግንኙነት እንዲጠናከር ላደረጉት አስተዋዕጾ በፓኪስታን መንግስት ምስጋና ቀረበላቸው።
አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፓኪስታን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሰይድ ዩሱፍ ራዛ ጊላኒ ጋር እያደገ በመጣው የሀገራቱ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ዙሪያ መክረዋል።
በዚህም በሰላምና ጸጥታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአቪዬሽን፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በቱሪዝምና በባህል ዘርፎች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በፓኪስታን ሴኔት የፈረንጆቹ ግንቦት 25 የፓኪስታን አፍሪካ የወዳጅነት ቀን እንዲሆን መወሰኑን ያስታወሱት አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር)፤ ይህም የተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ታላቅ አስተዋፅኦ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በፓኪስታን ለማስፈጸም ለተጫወቱት ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሰይድ ዩሱፍ ራዛ ጊላኒ በበኩላቸው፤ አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) የኢትዮ ፓኪስታን ግንኙነት እንዲጠናከር ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በፓኪስታን እንዲሰርጽ በማድረግ ሀገሪቱ እየተፈተነችበት ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመዋጋት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና ላሳዩት ንቁ ተሳትፎ ለአምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።
የሀገራቱ ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ እንዲሻገር መንግስታቸው የድርሻውን እንደሚወጣ ማረጋገጣቸውን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።