የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለ2 አሻጋሪ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ

By Melaku Gedif

October 02, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ፕሮጀክቶች የኢንዱስትሪ እድገትን ከማሳየት በላይ ናቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ዛሬ ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚያኮራ ታሪካዊ ሁነት ተፈፅሟል፤የሁለት አሻጋሪ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡

በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባው የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካና በጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ የሚገነባው የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ከሂላል የነዳጅ ስፍራ ድፍድፍ ነዳጅ በማውጣት፣ በማጣራትና በማጠራቀም በዓመት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የማዳበሪያ ፋብሪካው ከካሉብ የጋዝ ስፍራ በማውጣት እና 108 ኪሎ ሜትር የማጓጓዣ ቱቦ በመጠቀም በዓመት 3 ሚሊየን ቶን አምርቶ እንደሚያቀርብ አመልክተዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢንዱስትሪ እድገትን ከማሳየት በላይ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እድሎቻችንን የመጠቀም፣ ትብብሮችን የማጠናከርና ሰላምን የማጽናት የጋራ ኃላፊነታችንን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ስለሆነም ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በኅብረት እና በአንድነት ለእድገት መሰባሰባቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይሄን ስናደርግም እውነተኛውን የኢትዮጵያዊ ማንነት መንፈስ በሚያከብር መንገድ በዓለም መድረክ የኢትዮጵያን ሥፍራ ከፍ እናደርጋለን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ።