ፋና ስብስብ

የሰላም እና የዕርቅ ምልክት ሲንቄ …

By Yonas Getnet

October 02, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለኦሮሞ እናቶች በቁመታቸው ልክ በተዘጋጀች እና ቀጥ ካለ የተመረጠ የሃሮሬሳ ዘንግ የምትዘጋጅ የሲንቄ በትር ያገባች ሴት የምትይዘው ልዩ መለያቸው ናት።

የሲንቄ በትር በቀላሉ የማይሰበር፤ ልጃገረድ በሰርግ ቀን በእናቷ ለሙሽሪት የሚሰጥ የክብር ስጦታዋ ሲሆን በኦሮሞ ባሕል ውስጥ ትልቅ እና ልዩ ስፍራ ይሰጠዋል።

ይህች የሲንቄ በትር ለዕይታ እንድትማርክ እና ቀላ ብላ ውበትን እንድትላበስ እና ጥንካሬ እንዲኖራት በሳር ቤት ውስጥ ጭስ በሚያገኛት ቦታ ላይ ትቀመጣለች።

ሴቷ ሰላም የምታስከብርበት፣ ዕርቅንም የምታወርድበት የሲንቄ በትር በጸበኞች መካከል የሚንቀለቀልን ጠብ የማብረድ ኃይል አላት።

በሃደ ሲንቄዎች የምትያዝው ይህች የሰላም እና የዕርቅ ምልክት የሆነችው የሲንቄ በትር በጭራሽ እንስሳት አይመቱበትም።

በአካባቢው አለመግባባት ሲፈጠር ሃደ ሲንቄዎች በትራቸውን ይዘው እልልታ እያሰሙ በመውጣት በቀጥታ በጠበኞች መሀል በትራቸውን ይጥላሉ።

ይሄኔ ሁሉም ጸብ ይበርዳል፣ የተሰበቀ ጦርም ይመለሳል፣ ቁጣውም ቀዝቀዝ ይላል፤ ሲንቄውን ተሻግሮ ለዱላ መጋበዝ የሚታሰብ አይደለም፤ በትሯንም በጭራሽ አይሻገርም።

ሃደ ሲንቄ አረጋሽ ገዳ ከፋና ሚድያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ እኛ የተጣላውን በማስታረቅ እንዲዛመዱ እና ወንድማማችነትን እንዲፈጥሩ እናደርጋለን።

ሃደ ሲንቄ ማለት ለሁሉም ሰው በሙሉ ማንንም ሳትለይ በግልጽ እና በቅንነት የምትፈርድ ለዱር እንስሳ እንኳን የምትራራ እናት ናት ሲሉም ተናግረዋል።

የሲንቄ በትር የሰላም ምልክት እንደሆነች እና በተጣላ ሰው መሃል ከገባች አልፎ ለጸብ፣ ለመገዳደልም ሆነ ወደ ሌላ ርምጃ የሚገባ እንደሌለ ሃደ ሲንቄ በለጡ ይናገራሉ።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!