የሀገር ውስጥ ዜና

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

By Hailemaryam Tegegn

October 03, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፥ ኢሬቻ ፈጣሪን ማመስገኛ፣ ፍቅርንና እርቅን ማንፀባረቂያ፣ የአብሮነትና የተሰፋ ሐሴትን መጎናጸፊያ እንዲሁም ንፉግነትንና ጥላቻን ማከሚያ ትውፊት ሆኖ የሚያገለግል እሴት ነው ብለዋል፡፡

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ ኢሬቻ በኦሮሞ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሰላም የፍቅር የይቅርታ የአብሮነት በዓል መሆኑን አውስተዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፥ ኢሬቻ ዕርቅ፣ ይቅርታና ሰላም የሚነግስበት፣ ወንድማማችነት የሚጎለብትበትና ህብረ ብሔራዊነት የሚያብብበት የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በጋራ የሚያከብረው ታላቅ በዓል መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

‎የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፥ ኢሬቻ ወንድማማችነትና አብሮነት የበለጠ እንዲጎለብት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዓሉ የበለጠ እንዲተዋወቅና በአግባቡ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፥ የኦሮሞ የምስጋና ስርዓት ደምቆ የሚታይበት ይህን ታላቅ በዓል ስናከብር፥ የኢሬቻ ዋነኛ እሴት የሆኑትን ሰላም፥ ምህረት እና አንድነትን አጥብቆ መያዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥ ኢሬቻ የጨለማው ወቅት አልፎ ወደ ብሩህ ወቅት የመሸጋገሪያ ድልድይ መሆኑን ጠቅሰው፥ የበዓሉን የይቅርታ መንፈስ በመላ ሀገሪቱ በማስፈን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው፥ የኦሮሞ የምስጋና ስርዓት ደምቆ የሚታይበት ይህን ታላቅ በዓል ስናከብር፥ የኢሬቻ ዋነኛ እሴት የሆኑትን ሰላም፥ ምህረት እና አንድነትን አጥብቆ መያዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።