የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በሱዳን የተከሰተውን ጎርፍ ከሕዳሴ ግድብ ጋር በማያያዝ የቀረበውን ውንጀላ ውድቅ አደረገች

By Mikias Ayele

October 04, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሱዳን የተከሰተውን ጎርፍ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በማያያዝ ግብጽ ያቀረበችውን መሰረተ ቢስ ውንጀላ ውድቅ አደረገች፡፡

ግብጽ ከቀናት በፊት በውሃ እና መስኖ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ፥ ሰሞኑን በሱዳን የተከሰተው ጎርፍ በግድቡ የአስተዳደር ችግር የተፈጠረ ነው የሚል ውንጀላ አቅርባለች፡፡

የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከግብጽ በኩል የቀረበው ውንጀላ መሰረተ ቢስና ከእውነታው ጋር የሚጣረስ መሆኑን ገልጾ፥ ግድቡ ጎርፍ ከማስከተል ይልቅ የጎርፍ አደጋን መቀነስ እንዳስቻለ አስገንዝቧል፡፡

ሚኒስቴሩ በመግለጫው ኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን የመገንባትና የውሃ ፍሰታቸውን የማስተዳደር ልምድ እንዳላት ጠቅሶ፥ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገንባት በሱዳን እና ግብጽ ሊከሰት የሚችለውን ከፍተኛ ጎርፍ ማስቀረቱን አስረድቷል፡፡

ግድቡ ተመጣጣኝ የውሃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ በሱዳንና በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚደርሰውን አማካይ ከፍተኛ የጎርፍ መጠንና የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ አስችሏልም ነው ያለው፡፡

በክረምት ወራት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች የጣለው ዝናብ በሱዳንና ግብፅ በሰውና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ሊያስከትል የሚችል ጎርፍ ይከሰት እንደነበር ገልጿል፡፡

የሱዳን የግብርና እና መስኖ ሚኒስቴር በሀገሪቱ ለተከሰተው ጎርፍ የመሰረተ ልማት ችግርን ጨምሮ ምክንያት ያላቸውን ጉዳዮች በግልጽ አስቀምጧል፡፡

ነገር ግን ግብጽ ከዚህ በተቃራኒ የጎርፍ አደጋውን ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በማገናኘት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት ሀሰተኛ ክስ ኢትዮጵያ ላይ ማቅረቧን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመግለጫው አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ኃላፊነት የሚሰማት ሀገር እንደመሆኗ የሕዳሴ ግድብን የውሃ ፍሰት በተመለከተ ከጎረቤት ሱዳን ጋር የመረጃ ልውውጥና ትብብር ለማድረግ ማዕቀፍ ዘርግታ እየሰራች እንደምትገኝ ጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን በመገንባት ልምድ ያላት ሀገር ናት ያለው ሚኒስቴሩ÷ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግድቦችን የውሃ ፍሰትና ቴክኒካል ስራዎችን በሚገባ እያስተዳደረች እንደምትገኝ አስታውቋል፡፡

ግብጽ ለጎረቤት ሀገራት ተቆርቋሪ በመምሰል ያወጣችውን የሀሰት ውንጀላና የስም ማጥፋት መግለጫን ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንደምታደርግ ሚኒስቴሩ አረጋግጧል፡፡