አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ፖሊስ በክልሉ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ አያሌ መሥዋዕትነቶችን ከፍሏል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት የሚሰጥ የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት÷ የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ማማ የማይወርድ የኢትዮጵያ አካል ነው ብለዋል።
ክልሉ በአንድ በኩል ከጽንፈኛ፣ ከባንዳና ከባዳ ጋር በመታገል በሌላ በኩል ብልጽግናን ለማምጣት ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ጋር በመፋለም መንታ ድል አያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ በክልሉ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሰላምና ደኅንነትን ለመጠበቅ አያሌ መሥዋዕትነቶችን ከፍሏል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ከወንጀለኞች፣ ከጽንፈኞች፣ ከሙሰኞች፣ ከኮንትሮባንዲስቶች፣ ከባንዳዎችና ከባዳዎች ጋር ተፋልሟል ብለዋል።
ፖሊሳዊ አደረጃጀቱን ብቃቱን እና ተቋማዊ ጥንካሬውን እንዲጠብቅ የተከናወነው ሪፎርም ውስጣዊ፣ ውጫዊና ተልዕኳዊ መልኮች ያሉት ነው ሲሉም አክለዋል።
ውስጣዊ በሆነው ሪፎርም መሠረት ተቋሙ ብቁ አደረጃጀት፣ አሠራር፣ ነጻነትና ገለልተኝነት እንዲሁም የፖሊስን ዶክትሪን እንዲከተል ለማድረግ ተሞክሯል፤ የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያው ተጠሪነት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆን ተደርጓልም ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት ባጸደቀው መዋቅራዊ አደረጃጀት ከክልል ጀምሮ በተዋረድ ባሉ የአመራርና የሙያተኛ የሥራ መደቦች ሥራ እና ሠራተኛን ለማገናኘት በሚያስችል መልኩ የአመራር ብቃትን፣ ሥነ ምግባርን እና የትምህርት ዝግጅትን መሠረት ያደረገ ምደባ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር ገብቷል ሲሉም ጠቅሰዋል።
ውጫዊ በሆነው ሪፎርም መሠረት ደግሞ የዞን ፖሊስ መምሪያ እና የወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶችን ቢሮዎች ለሥራ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ የሕንጻ ዲዛይን ተዘጋጅቶ በሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ ዓይነት የቢሮ ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅቶች መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡
በክልል ደረጃ የጀግኖች ማዕከል ግንባታን ለማስጀመር በደብረ ብርሃን ከተማ ግንባታ መጀመሩን እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅን ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ከፍ እንዲል ለማድረግ የሚያስችል የዐዋጅ ማሻሻያ በክልሉ ምክር ቤት መጽደቁን አመላክተዋል።
እንደዚሁም ተልዕኳዊ በሆነው ሪፎርም ሰላም የማስፈን ሥራ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር፣ ግጭቶችን ለመከላከል እና ሕገ ወጥ የወንጀል ድርጊት ለመቆጣጠር በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ በነገው የክልሉ ታሪክ ክልሉን ከባዳና ከባንዳ ተከላክሎ ለዕድገት፣ በማብቃቱ ላመነበትና ቃል ለገባለት ተልዕኮ ሲባል መሥዋዕትነት መክፈል እና ልቡ፣ አስተሳሰቡ እና እጁ ከጽንፈኝነት፣ ከጎጠኝነት፣ ከሌብነት የጸዳ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል።
አሁን የጀመርነው ሪፎርም ዋና ዓላማ በእነዚህ በሦስቱ ዕሴቶች ታሪኩን በአማራ ክልል የሚጽፍ የፖሊስ ኃይል ለማፍራት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በክልሉ በጸረሰላም ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጡና ለመነጋገር ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
ጫካ ያሉ ጸረ ሰላም ኃይሎች ከተላላኪነት ወጥተው ለክልሉ ሰላም በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።
በለይኩን ዓለም
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!