አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ከወጪ ንግድ አግኝታለች አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ በግብርናው ዘርፍ በ2017 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ምርት መመረቱን ገልጸው፥ ይህም ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸር የ27 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ59 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማደጉን ጠቅሰው፥ የወርቅ ምርት በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 9 ቶን በ2017 በጀት ዓመት ወደ 38 ነጥብ 87 ቶን አድጓል ብለዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን የነበረው የሲሚንቶ ምርት በ2017 በጀት ዓመት ወደ 9 ነጥብ 1 ሚሊየን ቶን አድጓል ነው ያሉት፡፡
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የዲጂታል ኢኮኖሚ አመላካቾች በከፍተኛ ሁኔታ እድገት ማሳየታቸውን እንዲሁም የባንክ ብድር 822 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መለቀቁን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ከውጪ ንግድ ማግኘቷን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ ከ2016 በጀት ዓመት የ116 በመቶ ብልጫ ያሳየ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በተደረገው ተከታታይ ጥረት የዋጋ ንረት በ2016 ሰኔ ወር ከነበረው የ19 ነጥብ 9 በመቶ በ2017 ዓ.ም ተመሳሳይ ወር ላይ 13 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል።
ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ በማድረግ 4760 ብር የነበረውን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ወደ 6000 ብር ማሳደግ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በ2017 በጀት ዓመት መንግስት ከብሔራዊ ባንክ ምንም አይነት የቀጥታ ብድር ሳይወስድ የበጀት ዓመቱን ማጠናቀቁን ገልጸው፥ ይህም ታላቅ ቁምነገር ነው ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በኢትዮጵያ መካሄዳቸውን ነው ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ የገለጹት፡፡
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!