የሀገር ውስጥ ዜና

የፐልስ ኦፍ አፍሪካ መቋቋም የአፍሪካን ድምጽ በዓለም መድረክ የማሰማት መሠረት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

October 07, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ መቋቋም ጠንካራና ቱባውን የአፍሪካ ድምጽ በዓለም መድረክ የማሰማት መሠረት ነው አሉ፡፡

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ በተሰኘው የፓን አፍሪካ ሚዲያ የሥራ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የሚዲያው መቋቋም አፍሪካን በአሉታዊ ገጽታ የማቅረብ ሥራን ለመመከትና የራሳችንን ትርክት በራሳችን የመቅረጽ ተግባራችንን የምናፀናበት ጠቃሚ ርምጃ ነው ብለዋል።

አፍሪካ ሰፊ እና እምቅ ሀብት ያላት አኅጉር መሆኗን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ እንደ አነስተኛና አቅመቢስ ተደርጋ እንደምትሳል ጠቅሰዋል።

የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ አነስተኛ ግን እጅግ ትርጉም ያለው ጅማሮ በመጪዎቹ ጊዜያት ከፍ ወዳለ መሪ አኅጉራዊ ሚዲያ የማደግ መንገድ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል።

አፍሪካ በማያጠራጥር መንገድ ዐቢይ የኢንድስትሪ ማዕከል እና የዓለም ቁልፍ ሚና ተጫዋች የመሆን መንገድ ላይ እየተጓዘች እንደምትገኝ ጠቅሰው፥ የሚዲያው መቋቋም ወደፊት የመመልከት ርምጃ ነው ብለዋል።