አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር በሀላባ እና ከምባታ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረክበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ መንደሮቹ የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻል የምናደርገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ጅማሮ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቤቶቹ የፀሃይ ኃይል ማመንጫ የተገጠመላቸው፣ ለማብሰል ደግሞ ከእንስሳት እዳሪ ባዮጋዝ የሚጠቀሙ፣ የተለየ ሳሎን፣ መጸዳጃ እና ሰርቪስ ቤቶች የተሟላላቸው መሁናቸውንም ጠቁመዋል።
ንጽህናን በሚያረጋግጥ እና የአኗኗር ደረጃን ከፍ በሚያደርግ አኳኋን የተለየ የእንስሳት በረት ተሰርቶላቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እነዚህ የገጠር ኮሪደር ልማት መንደሮች የገጠሩን አኗኗር የማሳደግ ሕልማችን አካል በመሆን ተስፋፍተው የሚሰሩ ይሆናል ብለዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የክረምት በጎ ፈቃድ በከተሞች ለሚኖሩ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች መኖሪያ ቤቶችን ስናቀርብ ቆይተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ አሁን ደግሞ በገጠር ኮሪደር ልማት የሥራውን እመርታ ወደገጠር አስፋፍተናል ሲሉም አብራርተዋል።
ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና የዲያስፖራው ማኅበረሰብ እነኚህን ሥራዎች እንዲደግፉ እና እንዲሳተፉ አበረታታለሁ ሲሉም አክለዋል።
ባለፈው ጉብኝቴ ወቅት ያቀረብኩላቸውን የቤት ሥራ በመወጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ በራስ አቅም የሀምበሪቾ ተራራ ደረጃንም በእጥፍ ሠርተው ላጠናቀቁት አመራሮች ያለኝን ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
ወደፊትም የየአካባቢ አመራሮች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሠሩትን ሞዴል መንደሮች በመጪው ዓመት በየዞኑ ወደ 100 ቤቶች እንዲያሳድጉ አሳስባለሁም ነው ያሉት።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!